አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 22 2002 (ሬዲዮ ፋና) የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በህገ ወጥ ኤጄንሲዎች ላይ እርምጃ መውሰድ መጀመሩን አስታወቀ።
የሰዎች ህገ ወጥ ዝወውር እንደማንኛውም ህገ ወጥ ድርጊት ተቆጥሮ ጠንካራ አቋም መያዙንና በህገ ወጥ መንገድ የሚንቀሳቀሱትን ለመገደብም በአዋጁ መሰረት አስተዳደራዊ እርምጃ መወሰድ መጀመሩን በሚኒስቴሩ የስራ ስምሪት አገልግሎት ማስፋፊያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አበበ ሃይሌ ገልጸዋል።
የግንዛቤ ማስጨበጫ የተለያዮ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሆነና ከህጋዊ ኤጄንሲዎች ጋር በመተባበር ለችግሩ መፍትሄ የሚሆን ተግባር በመከናወን ላይ መሆኑን ጠቁመው ኤጄንሲዎች ህግን አክብረው እንዲሰሩ ጥረት መደረጉንም አብራርተዋል።
ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ ሀገር ኤጄንሲዎች ጋር ተባብሮ በመስራት እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑንና ችግሩን በዘላቂነት ለማስቆምም የክትትልና ቁጥጥር ስራ እየተካሄደ መሆኑም ተመልክቷል።
እስካሁን ድረስም 54 ኤጀንሲዎች በህጋዊነት ተመዝግበው እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን የባልደረባችን እመርታ አስፋው ዘገባ ያመለክታል።